12 August 2026
Ministry of Water and Energy – Ethiopia
ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) – የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ከቢጌታ ቢዝነስ ኃ.የተ.የግ.ማህበር ጋር የ933,609,566.54 ብር የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ግንባታ ሥራ የውል ስምምነት ፈርመዋል።

የፕሮጀክቱ ትግበራ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከምባታ ዞን፣ አንጋጫ ወረዳ የሚከናወን ሲሆን፣ ወጪውም በመንግሥት በሚመደብ በጀት የሚሸፈን ነው።
በውሉ መሠረት ሥራው በ18 ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ የሲቪል ግንባታ ሥራዎችን ጨምሮ የውሃ ቧንቧዎች፣ መገጣጠሚያዎችና የቫልቭ መለዋወጫዎች አቅርቦት፣ እንዲሁም የኤሌክትሮ-ሜካኒካል መሣሪያዎች ግዥና ተከላ ይካተታሉ።
ፕሮጀክቱ በCR-WASH መርሃ ግብር ሥር የሚተገበር ሲሆን፣ በአካባቢው የውሃ አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለማሻሻል ያለመ ነው። በተለይም ለሕብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማሳደግ የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
የሥራው ተቋራጭ ቀደም ሲል በተመሳሳይ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ የሥራ ልምድ ያካበተ መሆኑ ታውቋል።
በውል ስምምነቱ ወቅት ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ፣ ተቋራጩ የተወሰኑትን የጥራት መስፈርቶች በጥብቅ በመከተል ሥራውን በተያዘለት ጊዜ እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል። ፕሮጀክቱ ለሕዝብ ዘላቂ ጥቅም እንዲያስገኝ በሥራ አፈጻጸሙ ላይ ትኩረት እንዲደረግም ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በበኩሉ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም በቅርበት በመከታተል ሥራው በውሉ መሠረት እንዲከናወን እንደሚያደርግ ገልጿል።
የሥራው ተቋራጭም ለተሰጠው የሥራ ዕድል ምስጋና በማቅረብ፣ ፕሮጀክቱን በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ፣ የጥራት መስፈርቶችን በማሟላት ለማጠናቀቅና ለማስረከብ ቃል ገብቷል።


ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p
ቴሌግራም
ዌብሳይት
X/ትዊተር
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ